Wednesday, February 17, 2010

መጽሐፈ ዕዝራ 1

ምዕራፍ 1።

1፤ በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ።

2፤ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል። የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤

3፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእንናተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤

4፤ በሚኖርበትም ስፍራ ሁሉ ለቀረው ሰው የአገሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፤ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት ሌላ ይሁን።

5፤ የይሁዳና የብንያም የአባቶች ቤቶች አለቆችም፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ።

6፤ በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት ሁሉ ሌላ በብር ዕቃና በወርቅ በገንዘቦችና በእንስሶች በሌላም ስጦታ አገዙአቸው።

7፤ ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች አወጣ።

8፤ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገቡ ላይ በነበረው በሚትሪዳጡ እጅ አወጣቸው፥ ለይሁዳም መስፍን ለሰሳብሳር ቈጠራቸው።

9፤ ቍጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ አንድ ሺህም የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝም ቢላዎች፥

10፤ ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ አሥርም ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ።

11፤ የወርቁና የብሩ ዕቃዎች ሁሉ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ፤ እነዚህንም ሁሉ ሰሳብሳር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ምርኮኞቹ ጋር ወሰደ።

መጽሐፈ ዕዝራ 2

ምዕራፍ 2።

1፤ የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን ከማረካቸው ምርኮኞች ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ወደ እየከተማቸው የተመለሱት የአገር ልጆች እነዚህ ናቸው።

2፤ ከዘሩባቤል፥ ከኢያሱ፥ ከነህምያ፥ ከሠራያ፥ ከረዕላያ፥ ከመርዶክዮስ፥ ከበላሳን፥ ከመሴፋር፥ ከበጉዋይ፥ ከሬሁም፥ ከበዓና ጋር መጡ።

3፤ የእስራኤልም ሕዝብ ሰዎች ቍጥር ይህ ነው፤ የፋሮስ ልጆች፥ ሁለት ሺህ መቶ ሰባ ሁለት።

4፤ የሰፋጥያስ ልጆች፥ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት።

5፤ የኤራ ልጆች፥ ሰባት መቶ ሰባ አምስት።

6፤ ከኢያሱና ከኢዮአብ ልጆች የሆኑ የፈሐት ሞዓብ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ አሥራ ሁለት።

7፤ የኤላም ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት።

8፤ የዛቱዕ ልጆች፥ ዘጠኝ መቶ አርባ አምስት።

9፤ የዘካይ ልጆች ሰባት መቶ ስድሳ።

10፤ የባኒ ልጆች፥ ስድስት መቶ አርባ ሁለት።

11፤ የቤባይ ልጆች፥ ስድስት መቶ ሀያ ሦስት።

12፤ የዓዝጋድ ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ ሀያ ሁለት።

13፤ የአዶኒቃም ልጆች፥ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት።

14፤ የበጉዋይ ልጆች፥ ሁለት ሺህ አምሳ ስድስት።

15፤ የዓዲን ልጆች፥ አራት መቶ አምሳ አራት።

16፤ ከሕዝቅያስ ወገን የአጤር ልጆች፥ ዘጠና ስምንት።

17፤ የቤሳይ ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ ሦስት።

18፤ የዮራ ልጆች፥ መቶ አሥራ ሁለት።

19፤ የሐሱም ልጆች፥ ሁለት መቶ ሀያ ሦስት።

20፤21፤ የጋቤር ልጆች፥ ዘጠና አምስት። የቤተ ልሔም ልጆች፥ መቶ ሀያ ሦስት።

22፤ የነጦፋ ሰዎች፥ አምሳ ስድስት።

23፤ የዓናቶት ሰዎች፥ መቶ ሀያ ስምንት።

24፤ የዓዝሞት ልጆች፥ አርባ ሁለት።

25፤ የቂርያትይዓሪምና የከፊራ የብኤሮትም ልጆች፥ ሰባት መቶ አርባ ሦስት።

26፤ የራማና የጌባ ልጆች፥ ስድስት መቶ ሀያ አንድ።

27፤ የማክማስ ሰዎች፥ መቶ ሀያ ሁለት።

28፤ የቤቴልና የጋይ ሰዎች፥ ሁለት መቶ ሀያ ሦስት።

29፤ የናባው ልጆች፥ አምሳ ሁለት።

30፤ የመጌብስ ልጆች፥ መቶ አምሳ ስድስት።

31፤ የሁለተኛውም ኤላም ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት።

32፤ የካሪም ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ።

33፤ የሎድና የሐዲድ የኦኖም ልጆች፥ ሰባት መቶ ሀያ አምስት።

34፤ የኢያሪኮ ልጆች፥ ሦስት መቶ አርባ አምስት።

35፤ የሴናዓ ልጆች፥ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ።

36፤ ካህናቱ፤ ከኢያሱ ወገን የዮዳኤ ልጆች፥ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሦስት።

37፤ የኢሜር ልጆች፥ ሺህ አምሳ ሁለት።

38፤ የፋስኮር ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት።

39፤ የካሪም ልጆች፥ ሺህ አሥራ ሰባት።

40፤ ሌዋውያኑ፤ ከሆዳይዋ ወገን የኢያሱና የቀድምኤል ልጆች፥ ሰባ አራት።

41፤ መዘምራኑ፤ የአሳፍ ልጆች፥ መቶ ሀያ ስምንት።

42፤ የበረኞች ልጆች፤ የሰሎም ልጆች፥ የአጤር ልጆች፥ የጤልሞን ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የሐጢጣ ልጆች፥ የሶባይ ልጆች፥ ሁሉ መቶ ሠላሳ ዘጠኝ።

43፤ ናታኒም፤ የሲሐ ልጆች፥ የሐሡፋ ልጆች፥

44፤ የጠብዖት ልጆች፥ የኬራስ ልጆች፥ የሲዓ ልጆች፤

45፤ የፋዶን ልጆች፥ የልባና ልጆች፥

46፤ የአጋባ ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የአጋብ ልጆች፥ የሰምላይ ልጆች፥ የሐናን ልጆች፥

47፤ የጌዴል ልጆች፥ የጋሐር ልጆች፥ የራያ ልጆች፥

48፤ የረአሶን ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥

49፤ የጋሴም ልጆች፥ የዖዛ ልጆች፥ የፋሴሐ ልጆች፥

50፤ የቤሳይ ልጆች፥ የአስና ልጆች፥ የምዑናውያን ልጆች፥ የንፉሰሲም ልጆች፥

51፤ የበቅቡቅ ልጆች፥ የሐቁፋ ልጆች፥ የሐርሑር ልጆች፥

52፤ የበስሎት ልጆች፥ የምሒዳ ልጆች፥

53፤ የሐርሳ ልጆች፥ የበርቆስ ልጆች፥

54፤ የሲሣራ ልጆች፥ የቴማ ልጆች፥ የንስያ ልጆች፥ የሐጢፋ ልጆች።

55፤ የሰሎሞንም ባሪያዎች ልጆች፤ የሶጣይ ልጆች፥ የሶፌሬት ልጆች፥ የፍሩዳ ልጆች፥

56፤ የየዕላ ልጆች፥ የደርቆን ልጆች፥ የጌዴል ልጆች፥

57፤ የሰፋጥያስ ልጆች፥ የሐጢል ልጆች፥ የፈክራት ልጆች፥ የሐፂቦይም ልጆች፥ የአሚ ልጆች።

58፤ እነዚህ ናታኒም ሁሉና የሰሎሞን ባሪያዎች ልጆች ሦስት መቶ ዘጠና ሁለት ነበሩ።

59፤ ከቴልሜላ፥ ከቴላሬሳ፥ ከክሩብ፥ ከአዳን፥ ከኢሜር የወጡ እነዚህ ነበሩ፤ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ቤቶችና ዘራቸውን ወይም ከእስራኤል ወገን መሆናቸውን ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም፤

60፤ የዳላያ ልጆች፥ የጦብያ ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ ሁለት ነበሩ።

61፤ ከካህናቱም ልጆች፤ የኤብያ ልጆች፥ የአቆስ ልጆች፥ ከገለዓዳዊው ከቤርዜሊ ልጆች ሚስት ያገባ፥ በስሙም የተጠራ የቤርዜሊ ልጆች።

62፤ እነዚህ በትውልድ መጽሐፍ ትውልዳቸውን ፈለጉ፤ ነገር ግን አልተገኘም፥ ከክህነትም ተከለከሉ።

63፤ ሐቴርሰታም። በኡሪምና በቱሚም የሚፈርድ ካህን እስኪነሣ ድረስ ከቅዱሰ ቅዱሳን አትበሉም አላቸው።

64፤65፤ ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ከነበሩ ከሎሌዎቻቸውና ከገረዶቻቸው ሌላ ጉባኤው ሁሉ አርባ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ነበሩ። ሁለት መቶም ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩአቸው።

66፤ ፈረሶቻቸውም ሰባት መቶ ሠላሳ ስድስት በቅሎቻቸውም ሁለት መቶ አርባ አምስት፥

67፤ ግመሎቻቸውም አራት መቶ ሠላሳ አምስት፥ አህዮቻቸውም ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ሀያ ነበሩ።

68፤ በኢየሩሳሌምም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ ጊዜ ከአባቶች ቤቶች አለቆች አያሌዎች ለእግዚአብሔር ቤት በስፍራው ይሠራ ዘንድ በፈቃዳቸው ሰጡ።

69፤ ስድሳ አንድ ሺህም የወርቅ ዳሪክ፥ አምስት ሺህም ምናን ብር፥ አንድ መቶም የካህናት ልብስ እንደ ችሎታቸው ወደ ሥራው ቤተ መዛግብት አቀረቡ።

70፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም፥ ከሕዝቡም አያሌዎች፥ መዘምራኑና በረኞቹም፥ ናታኒምም በከተሞቻቸው፥ እስራኤልም ሁሉ በከተሞቻቸው ተቀመጡ።

መጽሐፈ ዕዝራ 3

ምዕራፍ 3።

1፤ ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ልጆች በከተሞቻቸው ሳሉ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።

2፤ የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ ወንድሞቹም ካህናቱ፥ የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል ወንድሞቹም ተነሥተው በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ።

3፤ በአገሩም ካሉት አሕዛብ ፈርተው ነበርና መሠዊያውን በስፍራው ላይ አስቀመጡት፥ በጥዋትና በማታም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡበት።

4፤ እንደ ተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ፤ እንደ ሥርዓቱም ለየዕለቱ የተገባውን የየዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በቍጥር አቀረቡ።

5፤ ከዚያም በኋላ ዘወትር የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የመባቻውንም መሥዋዕት፥ የተቀደሱትንም የእግዚአብሔር በዓላት ሁሉ መሥዋዕት፥ ሰውም ሁሉ ለእግዚአብሔር በፈቃድ የሰጠውን ቍርባን አቀረቡ።

6፤ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ፤ የእግዚአብሔር መቅደስ ገና አልተመሠረተም ነበር።

7፤ ለጠራቢዎችና ለአናጢዎችም ገንዘብ ሰጡ፤ የፋርስም ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ በባሕር ወደ ኢዮጴ ያመጡ ዘንድ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎች መብልና መጠጥ ዘይትም ሰጡ።

8፤ በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፥ የኢዩሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ካህናትና ሌዋውያን፥ ወደ ኢየሩሳሌምም የተመለሱት ምርኮኞች ሁሉ ጀመሩ፤ ሌዋውያንንም ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ እንዲያሠሩት ሾሙአቸው።

9፤ ኢያሱም ልጆቹም ወንድሞቹም፥ የይሁዳም ልጆች ቀድምኤልና ልጆቹ፥ የኤንሐዳድም ልጆች፥ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ያሠሩ ዘንድ በአንድነት ቆሙ።

10፤ አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ በመሠረቱ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው መለከቱን ይዘው፥ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዓት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ።

11፤ ደግሞ። ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እያሉ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በእርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት ስለ ተመሠረተ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል አሉ።

12፤ የፊተኛውን ቤት ያዩ ሽማግሌዎች የሆኑ ብዙ ካህናትና ሌዋውያን የአባቶችም ቤቶች አለቆች ግን ይህ መቅደስ በፊታቸው በተመሠረተ ጊዜ በታላቅ ድምፅ ያለቅሱ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም በደስታ ይጮኹ ነበር፤

13፤ ደስ ብሎአቸው የሚጮኹትን ድምፅ ከሕዝቡ ልቅሶ ድምፅ መለየት የሚችል አልነበረም፤ ሕዝቡም በታላቅ ድምፅ ይጮኽ ነበር፥ ድምፁም ከሩቅ ይሰማ ነበር።

መጽሐፈ ዕዝራ 4

ምዕራፍ 4።

1፤ የይሁዳና የብንያምም ጠላቶች ምርኮኞቹ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መቅደስ እንደ ሠሩ ሰሙ።

2፤ ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች ቤቶች አለቆች ቀርበው። የአሦር ንጉሥ አስራዶን ወደዚህ ካመጣን ቀን ጀምሮ ለአምላካችሁ እንሠዋለንና፥ እንደ እናንተም እንፈልገዋለንና ከእናንተ ጋር እንሥራ አሉአቸው።

3፤ ዘሩባቤልና ኢያሱም የቀሩትም የእስራኤል አባቶች ቤቶች አለቆች። የአምላካችንን ቤት መሥራት ለእኛና ለእናንተ አይደለም፤ እኛ ለብቻችን ግን የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዳዘዘን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት እንሠራለን አሉአቸው።

4፤ የምድሩም ሕዝብ የይሁዳን ሕዝብ እጅ ያደክሙ ነበር፥ እንዳይሠሩም አስፈራሩአቸው፥

5፤ ምክራቸውንም ያፈርሱ ዘንድ በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ ዘመን ሁሉ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት ድረስ መካሪዎችን ገዙባቸው።

6፤ በአርጤክስስም መንግሥት፥ በመንግሥቱም በመጀመሪያ ዘመን፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ላይ የክስ ነገር ጻፉ።

7፤ በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፥ ሚትሪዳጡ፥ ጣብኤል ተባባሪዎቹም ለፋርስ ንጉሥ ለአርጤክስስ ጻፉ፤ ደብዳቤውም በሶርያ ፊደልና በሶርያ ቋንቋ ተጽፎ ነበር።

8፤ አዛዡ ሬሁም ጸሐፊውም ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ።

9፤ አዛዡ ሬሁም ጸሐፊውም ሲምሳይ የቀሩትም ተባባሪዎቻቸው፥ ዲናውያን፥ አፈርሳትካውያን፥ ጠርፈላውያን፥ አፈርሳውያን፥ አርካውያን፥ ባቢሎናውያን፥ ሱስናካውያን፥ ዴሐውያን፥ ኤላማውያን፥

10፤ ታላቁና ኃይለኛው አስናፈር ያፈለሳቸው በሰማርያና በወንዝ ማዶ ያኖራቸው የቀሩትም አሕዛብ ደብዳቤውን ጻፉ።

11፤ ለንጉሡ ለአርጤክስስ የላኩት የደብዳቤ ግልባጭ ይህ ነው። በወንዝ ማዶ ያሉት ሰዎች ባሪያዎችህ፤

12፤ አሁንም ከአንተ ዘንድ የወጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጡ ንጉሡ ይወቅ፤ ዓመፀኛይቱንና እጅግም የከፋቺቱን ከተማ ይሠራሉ፥ ቅጥርዋንም ያድሳሉ፥ መሠረትዋንም ጠገኑ።

13፤ አሁንም ይህች ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይሰጡ፥ የንጉሡም ግቢው እንዲጐድል ንጉሡ ይወቅ።

14፤ የንጉሡንም ጨው እንበላለንና፥ ንጉሡንም ሲያቃልሉት ማየት አይገባንምና ስለዚህ ልከን ለንጉሡ አስታውቀናል፤

15፤ በአባቶችህ ታሪክ መጽሐፍ ምርመራ ይደረግ፤ በዚያም በታሪክ መጽሐፍ ይህች ከተማ ዓመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጐዳች፥ ከጥንቱም ሽፍትነት በእርስዋ እንደ ተጀመረ ታገኛለህ፥ ታውቃለህም፤ ስለዚህም ይህች ከተማ ፈርሳ ነበር።

16፤ ይህችም ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ በወንዝ ማዶ ክፍል እንደሌለህ ለንጉሡ እናስታውቃለን።

17፤ ንጉሡም ለአዛዡ ለሬሁም፥ ለጸሐፊውም ለሲምሳይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶም ለተቀመጡ ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ።

18፤ ሰላም፤ አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ ተተርጕሞ ተነበበ።

19፤ እኔም አዝዣለሁ፥ ተመረመረም፤ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዓመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርስዋም ዓመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ።

20፤ በኢየሩሳሌምም እጅግ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ፥ በወንዝም ማዶ ያለውን አገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና ቀረጥን መጥንንም ይቀበሉ ነበር።

21፤ አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ እኔም እስካዝዝ ድረስ ይህች ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ።

22፤ ቸልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ለነገሥታቱ ጉዳትና ጥፋት እየበዛ ስለ ምን ይሄዳል?

23፤ የንጉሡም የአርጤክስስ ደብዳቤ ግልባጭ በሬሁምና በጸሐፊው በሲምሳይ በተባባሪዎቻቸውም ፊት በተነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ ሄዱ፤ በግድና በኃይልም አስተዉአቸው።

24፤ በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ቀረ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተጓጐለ።

መጽሐፈ ዕዝራ 5

ምዕራፍ 5።

1፤ ነቢያቱም ሐጌና የአዶ ልጅ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩ አይሁድ በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው።

2፤ በዚያን ጊዜ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ ተነሥተው በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመሩ፤ የሚያግዙአቸውም የእግዚአብሔር ነቢያት ከእነርሱ ጋር ነበሩ።

3፤ በዚያም ዘመን በወንዝ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ ሰተርቡዝናይ፥ ተባባሪዎቻቸውም ወደ እነርሱ መጥተው። ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንኑም ቅጥር ታድሱ ዘንድ ያዘዛችሁ ማን ነው? አሉአቸው።

4፤ ደግሞም። ይህንስ ሥራ የሚሠሩት ሰዎች ስም ማን ነው? ብለው ጠየቁአቸው።

5፤ የአምላካቸው ዓይን ግን በአይሁድ ሽማግሌዎች ላይ ነበረ፥ ይህም ነገር ወደ ዳርዮስ እስኪደርስ ድረስ፥ መልሱም በደብዳቤ እስኪመጣ ድረስ አልከለከሉአቸውም።

6፤ በወንዙ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ ተባባሪዎቹም በወንዙ ማዶ የነበሩት አፈርስካውያን ወደ ንጉሡ ወደ ዳርዮስ የላኩት የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነበረ።

7፤ እንዲህም የሚል ደብዳቤ ላኩለት። ለንጉሡ ለዳርዮስ ሙሉ ሰላም ይሁን፤

8፤ ወደ ይሁዳ አገር ወደ ታላቁም አምላክ ቤት እንደ ሄድን ንጉሡ ይወቅ፤ እርሱም በትልቅ ድንጋይ ተሠራ፥ በቅጥሩም ውስጥ እንጨት ተደረገ፥ ያም ሥራ በትጋት ይሠራል፥ በእጃቸውም ይከናወናል።

9፤ እነዚያንም ሽማግሌዎች። ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንስ ቅጥር ታድሱ ዘንድ ያዘዛችሁ ማን ነው? ብለን ጠየቅናቸው።

10፤ ደግሞም እናስታውቅህ ዘንድ፥ በእነርሱም ያሉትን ሹሞች ስም እንጽፍልህ ዘንድ ስማቸውን ጠየቅን።

11፤ እንደዚህም ብለው መለሱልን። እኛ የሰማይና የምድር አምላክ ባሪያዎች ነን፥ ከብዙም ዘመን ጀምሮ ተሠርቶ የነበረውን፥ ታላቁም የእስራኤል ንጉሥ ሠርቶ የፈጸመውን ቤት እንሠራለን።

12፤ አባቶቻችንም የሰማይን አምላክ ካስቈጡ በኋላ በከለዳዊው በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እርሱም ይህን ቤት አፈረሰ፥ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ።

13፤ ነገር ግን በባቢሎን ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ አዘዘ።

14፤ ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ የወሰደውን፥ ወደ ባቢሎንም መቅደስ ያፈለሰውን የእግዚአብሔርን ቤት የወርቅንና የብርን ዕቃ ንጉሡ ቂሮስ ከባቢሎን መቅደስ አውጥቶ ሰሳብሳር ለተባለው ለሹሙ ሰጠውና።

15፤ ይህን ዕቃ ይዘህ ሂድ፥ በኢየሩሳሌምም ባለው መቅደስ አኑረው፤ የእግዚአብሔርም ቤት በስፍራው ይሠራ አለው።

16፤ በዚያ ጊዜም ይህ ሰሳብሳር መጣ፥ በኢየሩሳሌምም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሠረተ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እየተሠራ አልተጨረሰም።

17፤ አሁንም ይህ ነገር በንጉሡ ዓይን መልካም ቢሆን ይህ የእግዚአብሔር ቤት በኢየሩሳሌም ይሠራ ዘንድ ከንጉሡ ከቂሮስ ታዝዞ እንደ ሆነ በባቢሎን ባለው በንጉሡ ቤተ መዛግብት ይመርመር፤ ስለዚህም ነገር ንጉሡ ፈቃዱን ይላክልን።

መጽሐፈ ዕዝራ 6

ምዕራፍ 6።

1፤ በዚያ ጊዜም ንጉሡ ዳርዮስ መዛግብት ባሉበት በባቢሎን ቤተ መጻሕፍት እንዲመረመር አዘዘ።

2፤ በሜዶን አውራጃ ባለው አሕምታ በሚባል ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅልል ተገኘ፥ በውስጡም ይህ ነገር ለመታሰቢያ ተጽፎ ነበር።

3፤ በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ እንዲህ ብሎ አዘዘ፤ በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት፥ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ፥ ይህ ቤት ይሠራ፥ በጽኑም ይመሥረት፤ ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን።

4፤ በሦስት ተራ ታላላቅ ድንጋይ፥ በአንድ ተራ እንጨት ይደረግ፤ ውጪውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ።

5፤ ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃ ይመለስ፤ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፥ በእግዚአብሔር ቤት ይኑር።

6፤ አሁንም አንተ በወንዝ ማዶ ያለኸው የአገሩ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻችሁ አፈርስካውያን፥ ከዚያ ራቁ፤

7፤ ይህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ ተዉ፤ የአይሁድም አለቃና የአይሁድም ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው ይሠሩ ዘንድ ተዉአቸው።

8፤ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን፥ በወንዝ ማዶ ካለው አገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጪውን በትጋት እንድትሰጡአቸው ሥራም እንዳታስፈቱአቸው አዝዣለሁ።

9፤ ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን፥ ወይፈኖችና አውራ በጎች ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌምም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው የወይን ጠጅና ዘይት ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ስጡአቸው።

10፤ ይኸውም ለሰማይ አምላክ ጣፋጭ ሽቱ የሆነውን መሥዋዕት ያቀረቡ ዘንድ ለንጉሡና ለልጆቹም ዕድሜ ይጸልዩ ዘንድ ነው።

11፤ ይህንም ትእዛዝ የሚለውጥ ሁሉ፥ ምሰሶው ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰቀልበት፤ ቤቱም የጉድፍ መጣያ ይደረግ ብዬ አዝዣለሁ።

12፤ ስሙንም በዚያ ያኖረው አምላክ ይህን ይለውጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ያፈርሱት ዘንድ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ ያጥፋ። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፤ በትጋት ይፈጸም።

13፤ ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም እንዲሁ ተግተው አደረጉ።

14፤ የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት ሠሩ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤልም አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስና እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስም ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ።

15፤ ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ።

16፤ የእስራኤልም ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ በደስታ አደረጉ።

17፤ በዚህም በእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ መቶ ወይፈኖችና ሁለት መቶ አውራ በጎች አራት መቶም ጠቦቶች አቀረቡ ፤ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ።

18፤ በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው ሌዋውያኑም በየክፍላቸው አቆሙ።

19፤ ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ።

20፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር፤ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፤ ለምርኮኞቹም ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም ፋሲካውን አረዱ።

21፤ ከምርኮም ተመልሰው የመጡት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኵሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉ፤

22፤ እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ።

መጽሐፈ ዕዝራ 7

ምዕራፍ 7።

1፤ ከዚህም ነገር በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ መንግሥት ዕዝራ የሠራያ ልጅ፥

2፤ የዓዛርያስ ልጅ፥ የኬልቅያስ ልጅ፥ የሰሎም ልጅ፥ የሳዶቅ ልጅ፥ የአኪጦብ ልጅ፥

3፤ የአማርያ ልጅ፥ የዓዛርያስ ልጅ፥ የመራዮት ልጅ፥

4፤ የዘራእያ ልጅ፥ የኦዚ ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥

5፤ የአቢሱ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የአልዓዛር ልጅ፥ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፥ ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወጣ፤

6፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ ነበረ፤ የአምላኩም የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና ንጉሡ የሻውን ሁሉ ሰጠው።

7፤ ከእስራኤልም ልጆች ከካህናቱም ከሌዋውያኑም ከመዘምራኑም ከበረኞቹም ከናታኒምም በንጉሡ በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት አያሌዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።

8፤ በንጉሡም በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ።

9፤ በመጀመሪያውም ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን ሊወጣ ጀመረ፥ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና በአምስተኛ ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ።

10፤ ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።

11፤ ንጉሡም አርጤክስስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ቃልና ለእስራኤል የሆነውን ሥርዓት ይጽፍ ለነበረው ለጸሐፊው ለካህኑ ለዕዝራ የሰጠው የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነው።

12፤ ከንጉሠ ነገሥት ከአርጤክስስ ለሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ለካህኑ ለዕዝራ፥ ሙሉ ሰላም ይሁን፤

13፤ በመንግሥቴ ውስጥ ካሉ ከእስራኤል ሕዝብ ከካህናቱና ከሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ የሚወድድ ሁሉ ከአንተ ጋር እንዲሄድ አዝዣለሁ።

14፤ በእጅህ እንዳለችው እንደ አምላክህ ሕግ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ትጐበኝ ዘንድ፥

15፤ ንጉሡንና አማካሪዎቹም መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው ያቀረቡትን ብርና ወርቅ፥

16፤ በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ የምታገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤት በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ትወስድ ዘንድ በንጉሡና በሰባቱ አማካሪዎች ተልከሃልና፤

17፤ ስለዚህ በዚህ ገንዘብ ወደፈኖችንና አውራ በጎችን ጠቦቶችንም የእህላቸውንና የመጠጣቸውን ቍርባን ተግተህ ግዛ፤ በኢየሩሳሌምም ባለው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው።

18፤ ከቀረውም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ ለማድረግ ደስ የሚያሰኛችሁን ነገር እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አድርጉ።

19፤ ስለ አምላክህም ቤት አገልግሎት የተሰጠህን ዕቃ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አሳልፈህ ስጥ።

20፤ ከዚህም በላይ ለማውጣት የሚያስፈልግህን ለአምላክህ ቤት የሚያሻውን ነገር ከንጉሡ ቤተ መዛግብት አውጣ።

21፤ እኔም ንጉሡ አርጤክስስ በወንዝ ማዶ ላሉት በጅሮንዶች ሁሉ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። የሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ካህኑ ዕዝራ ከእናንተ የሚፈልገውን ሁሉ አዘጋጁለት፤

22፤ እስከ መቶ መክሊት ብርም ቢሆን፥ እስከ መቶ የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት ቢሆን፥ ጨውም ያለ ልክ ቢሆን ስጡ።

23፤ በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ቍጣ እንዳይሆን፥ የሰማይ አምላክ ያዘዘው ሁሉ ለሰማይ አምላክ ቤት በሙሉ ይደረግ።

24፤ ደግሞም በካህናቱና በሌዋውያን በመዘምራኑም በበረኞቹም በናታኒምም በዚህም በእግዚአብሔር ቤት በሚሠሩ አገልጋዮች ላይ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይጣል ብለን እናስታውቃችኋለን።

25፤ አንተም ዕዝራ፥ በእጅህ እንዳለው እንደ አምላክህ ጥበብ መጠን በወንዝ ማዶ ባሉ ሕዝብ ሁሉ የአምላክህን ሕግ በሚያውቁ ሁሉ ላይ ይፈርዱ ዘንድ ዳኞችንና ፈራጆች አስነሣ፤ የማያውቁትንም አስተምሩአቸው።

26፤ የአምላክህንም ሕግ፥ የንጉሡንም ሕግ በማያደርግ ሁሉ ላይ ሞት ወይም ስደት ወይም ገንዘብን መወረስ ወይም ግዞት በፍጥነት ይፈረድበት።

27፤28፤ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ያሳምር ዘንድ እንደዚህ ያለውን ነገር በንጉሡ ልብ ያኖረ፥ በንጉሡም በአማካሪዎቹም በንጉሡም ኃያላን አለቆች ሁሉ ፊት ምሕረቱን ወደ እኔ የላከ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። እኔም በላዬ ባለችው በአምላኬ በእግዚአብሔር እጅ በረታሁ፤ ከእኔም ጋር እንዲወጡ ከእስራኤል ዘንድ አለቆችን ሰበሰብሁ።